የአማራ ክልል ምክር ቤት | መስከረም 30/2019 ዓ.ም. | ባሕር ዳር
የሰንደቅ ዓላማ ቀን ጥቅምት 2 በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ይከበራል/ የተከበሩ አቶ አማረ ሰጤ/
የአማራ ክልል ምክር ቤት | መስከረም 30/2019 ዓ.ም. | ባሕር ዳር
የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ አማረ ሰጤ፣ የሰንደቅ ዓላማ ቀንን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
የተከበሩ አቶ አማረ ሰጤ በመግለጫቸው፣ ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን አከባበር በአዋጅ ቁጥር 863/2006 እና በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 3 መሠረት በግልጽ እንደተደነገገ ገልጸዋል።
ባለፉት 18 ዓመታት በተለያዩ ዝግጅቶች ሲከበር የቆየው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን፣ በዚህ ዓመት ለ19ኛ ጊዜ «ሰንደቅ ዓላማችን ለሕብረ ብሔራዊ መግባባትና ለአንድነታችን» በሚል መሪ ሐሳብ ጥቅምት 2 በመላው ኢትዮጵያ፣ በክልላችንም ጭምር፣ ይከበራል። በዕለቱም ዜጎች በሰንደቅ ዓላማው ፊት በመቆም ቃለ መሐላ ይፈጽማሉ ብለዋል።
የሰንደቅ ዓላማ ቀን ዜጎች ለሀገራቸውና ለሰንደቅ ዓላማቸው ያላቸውን ፍቅርና ክብር የሚገልጹበት፣ የሀገራችንን አንድነትና ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያድሱበት ቀን ነው።
ዜጎች የሰንደቅ ዓላማ ቀንን ሲያከብሩ፣ የሰንደቅ ዓላማውን ምንነት፣ ክብርና ትርጉም በተገቢው ሁኔታ ማወቅ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የሀገራችን ሉዓላዊነት፣ ነፃነትና ክብር በብዙ ፈተናዎች የተሞላ የዘመናት ተጋድሎ የተረጋገጠ ነው። ስለሆነም የዘመኑ ትውልዶች የሀገርን ሉዓላዊነት ጥቅምና ቀጣይነት በተግባር የሚያሳይ ጽኑ አቋም ማሳየት አለባቸው። በተለይም የጋራ ሀገራዊ መግባባትን፣ ሕብረ ብሔራዊ ወንድማማችነትንና እህትማማችነትን በማጠናከር ብሔራዊ አንድነትን ማጽናት ይገባል ብለዋል።
በመቀጠልም፣ 19ኛው ብሔራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በክልሉ በሚገኙ ሁሉም የክልል ተቋማት፣ የከተማ አስተዳደሮች፣ የዞን አስተዳደሮችና በእነሱ ሥር በሚገኙ ወረዳዎች በድምቀት እንደሚከበር ገልፀው።
አከባበሩም የሰንደቅ ዓላማውን ምንነት፣ እሴትና ትርጉም፣ ወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታዎች፣ በሀገራዊ ለውጡ የተመዘገቡ ውጤቶችና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን የሚመለከቱ ውይይቶች ይካሄዳሉ። እንዲሁም ሰንደቅ ዓላማው የሚሰቀልባቸው ሥነ ሥርዓቶችና በሰንደቅ ዓላማው ፊት ቃለ መሐላ የሚፈጸምባቸው ዝግጅቶች በሁሉም ተቋማት ይካሄዳሉ። ዝግጅቶቹም የሀገር ፍቅርን በማጎልበትና ለሰንደቅ ዓላማው ያለውን ክብር በማጠናከር ረገድ ጉልህ ሚና ይኖራቸዋል ብለዋል።
